Uncategorized

በመስቃን እና ማረቆ ወረዳ በተከሰተ ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች እርዳታ በመዘግየቱ መቸገራቸውን ተናገሩ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 19 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በመስቃን እና በማረቆ ወረዳዎች መካከል በተከሰተ ግጭት ተፈናቅለው በቡታጅራ ከተማ በሚገኝ የመጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በመዘግየቱ መቸገራቸውን ተናገሩ።

በሀገራችን በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ግጭቶች ለዜጎች ሰላማዊ ኑሮ መሰናክል እየሆኑ ነው፤ በርካቶች ይፈናቀላሉ የህይዎት መጥፋትም ይከሰታል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ በሃገር ውስጥ ግጭት በሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ሶሪያን በመቅደም በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የእነዚህ ግጭቶች እና ብጥብጦች አስከፊነት በህዝቦች መካከል ለዘመናት የነበረውን አብሮነት እና አንድነት ጥያቄ ውስጥ በማስገባት፥ የሰላሙን ዘላቂነት እና አስተማማኝነት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥም እየከተተው ይገኛል።

ከሰሞኑም በመስቃን እና ማረቆ ወረዳዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭትም ዜጎች ለአመታት ከኖሩበት ቀየ ተፈናቅለው ኑሯቸውን በመጠለያ እንዲያደርጉም አስገድዷቸዋል።

በእምነት፣ በባህል በማህበራዊ እና በሌሎች የአብሮነት እሴቶች ተቆራኝቶ ልዩነት የማይታይበት ህብረተሰብ፥ በመካከሉ በገቡ አጥፊዎች በፈጠሩት ብጥብጥ የሰው ህይወት ጠፍቷል።

ከዚህ ባለፈም ለአመታት በልፋት የፈራ ንብረትም እንዳልነበር ሆኗል፤ ይህ ብጥብጥ እና ግጭት ያስከተለው ችግርም ተፈናቃዮቹ አሁን ላይ የሰው እጅ እየጠበቁ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ኑሯቸውን እንዲመሩ አድርጓቸዋል።

ተፈናቃዮቹ አሁን ላይ የእለት ጉርሳቸውን እና አልባሳትን ከቡታጅራ ከተማ አስተዳደር እና ከከተማው ነዋሪ እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከፌደራል መንግስት ምንም አይነት ድጋፍ እንዳላገኙ ይገልጻሉ።

እንደነዚህ አይነት ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ለተጎጅዎች በ72 ሰዓታት ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እንዲደርስ የሚደነግግ መመሪያ አለ።

ይህን ተከትሎም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የአስቸኳይ ምግብ እርዳታው ለምን ዘገየ ሲል ለመጠየቅ ወደ ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሸን አቅንቷል።

በኮሚሽኑ የሎጅስቲክስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አይድሩስ ሀሰን ከክልሉ መምጣት የነበረበት የእርዳታ ጥያቄ ቆይቶ በመድረሱ ምክንያት እርዳታ መዘግየቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይም በጉራጌ ዞን 3 መጠለያ ጣቢያዎች ከ32 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተፈናቃዮች የሚውል የምግብ እና ሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታዎች ካለፈው እሁድ ጀምሮ መጓጓዝ መጀመራቸውንም ነው የተናገሩት።

የመስቃን ወረዳ ምግብ ዋስትና እና አደጋ መከላከል ቢሮ ሀላፊ አቶ ወርቅነህ ጥላሁን በበኩላቸው፥ አሁን ላይ ከብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የቀረበ ምግብ፣ አልባሳት እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማከፋፈል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋም ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት መጀመሩን እና በቅርቡም አስፈላጊው ጥናት ተደርጎ ተጎጅዎች ወደ ቀያቸው እንደሚመለሱም አስረድተዋል።

ተፈናቃዮቹም መንግስት በዚህ ድርጊት እጁ ያለበትን ግለሰብ በህግ ተጠያቂ በማድረግ ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል።

 

 

 

 

 

በዳዊት በሪሁን

 

Source: fana bc

abu hanya
Founder of Al Nejash Media is a journalist(MA), with more than 9 years of professional career
http://www.alnejashmedia.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *